የእርጅና ቅናሽ” ሲቀር የመኪና ዋጋ ጨመረ .

Von DW

ኢትዮጵያ ያገለገሉ ዕቃዎችና ተሽከርካሪዎች ወደ ገበያው ሲገቡ ከሚከፈልባቸው ታክስ በእርጅናቸው ምክንያት የሚቀነሰውን የገንዘብ መጠን አስቀርታለች። የገቢዎች ሚኒስቴር ውሳኔውን በይፋ ለመኪና ነጋዴዎች ባያሳውቅም ተፅዕኖ ማሳደር ግን ጀምሯል። ገበያውን የሚያውቁ የቪትዝ ዋጋ እስከ 70 ሺሕ፤ የኮሮላ እስከ 90 ሺሕ ብር ሊጨምር ይችላል ብለዋል

የገቢዎች ሚኒስቴር ያገለገሉ ዕቃዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከሚከፈልባቸው ቀረጥ በእርጅናቸው ምክንያት ይደረግ የነበረውን ቅናሽ አስቀርቷል። ውሳኔው በቀጥታ ከሚመለከታቸው መካከል ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች አስመጪዎች ውሳኔው በይፋ እጃቸው አልደረሰም። አውቶ ኢቲ የተባለው የተሽከርካሪ መገበያያ ድረ-ገጽ መሥራች እና ባለቤት አቶ እዮብ ከበደ የገቢዎች ሚኒስቴር ውሳኔ ለገበያው “ዱብ እዳ ሆኗል” ሲሉ ይናገራሉ። “አገር ውስጥ መኪና ያስገቡ ሰዎች በአዲሱ ቀረጥ እንዲቀርጡ እየተደረገ ነው። ዛሬ ጉምሩክ ብትሔድ [መኪና አስመጪዎች] በአዲሱ ነው የምትስተናገዱት ተብለው መኪና እንዳይወጣ ተይዟል” የሚሉት አቶ እዮብ ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ ጭምር አዲሱ ውሳኔ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ውሳኔውን በይፋ ካላሳወቃቸው የተሽከርካሪ ነጋዴዎች መካከል አንዱ አቶ ኑረዲን ሬድዋን ናቸው። “በስሚ ስሚ ነው የሰማንው። ፎቶ የተነሳ ወረቀት ምናምን እንጂ ሙሉ መረጃው ወይም መመሪያው የለም” ሲሉ ይናገራሉ።

አቶ ሬድዋን የጠቀሱት እና በገቢዎች ሚኒስቴር ምኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ተፈርሞ የወጣ የተባለ ደብዳቤ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ሲዘዋወር ታይቷል። “የጸደቁ መመሪያዎች ስለመላክ” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይኸው ደብዳቤ ለጉምሩክ ኮሚሽን የተላከ እንደሆነ ይጠቁማል። በደብዳቤው “ማንኛውም ያገለገለ ዕቃ ተሽከርካሪን ጨምሮ ወደ አገር ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ቀረጥና ታክሱን ለመወሰን ምንም አይነት የእርጅና ቅናሽ አይደረግም።” የሚል ሐሳብ ተካቶበታል።

እስካሁን በነበረው በኢትዮጵያ መንግሥት አሰራር መሰረት የተሽከርካሪ ቀረጥ በመኪናው የሲሲ መጠን፣ በተመረተበት ጊዜ እና በተገዛበት ዋጋ ይተመናል። ከተመረተ አንድ አመት የሞላው ተሽከርካሪ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ከሚከፈለው ታክስ 10 በመቶ በእርጅና ሳቢያ ይቀነስለታል። ከተመረተ ሁለት አመት የሞላው ተሽከርካሪ የእርጅና ቅናሽ 20 በመቶ ነበር። ከሶስት አመት በላይ የሆናቸው ተሽከርካሪዎች ከሚከፈልባቸው ታክስ 30 በመቶ ቅናሽ ሲቀነስላቸው ቆይቷል።

https://www.dw.com/am/%E1%8B%A8%E1%8A%A5%E1%88%AD%E1%8C%85%E1%8A%93-%E1%89%85%E1%8A%93%E1%88%BD-%E1%88%B2%E1%89%80%E1%88%AD-%E1%8B%A8%E1%88%98%E1%8A%AA%E1%8A%93-%E1%8B%8B%E1%8C%8B-%E1%8C%A8%E1%88%98%E1%88%A8/a-48853321

Recommended For You

About the Author: admin