እስረኞች ከሚዲያ ጋር ቃለ ምልልስ እንዲያደርጉ ሕግ ሊወጣ ነው::

28 July 2019ዮሐንስ አንበርብር

እስረኞች ከሚዲያ ጋር ቃለ ምልልስ እንዲያደርጉና ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲጠበቁ የሚያስገድድ ሕግ ሊወጣ ነው

ሴት እስረኞች በየጊዜው ሕፃናት ልጆቻቸውን ከማረሚያ ቤት ወጥተው እንዲጎበኙ ይፈቅዳል

ፍርድ ቤቶች ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲጠበቁ ለጠየቁ እስረኞች ፍትሕ የመስጠት ግዴታ ይጣልባቸዋል

ታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞች እንደ ማንኛውም ዜጋ ከሚዲያ አካላት ጋር ቃለ መጠይቅ የማድረግ፣ ሰብዓዊ ክብርን ከሚያዋርድ፣ ጭካኔ ከተሞላበትና ጤንነታቸውን አደጋ ላይ ከሚጥል አያያዝ የመጠበቅ መብታቸውን የሚያረጋግጥ አዋጅ ሊወጣ ነው፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርን በአዲስ መልክ የሚያቋቁመው አዋጅ፣ በዋናነት የታራሚዎችና የቀጠሮ እስረኞች ሰብዓዊ ክብሮችና መብቶች በአስገዳጅነት ለማስከበር የታለመ መሆኑን የተገኘው የሰነድ መረጃ ያመለክታል፡፡ ታራሚዎችና እስረኞች ሰብዓዊ ክብራቸውን ከሚያዋርድ፣ ጭካኔ ከተሞላበትና ጤንነታቸውን አደጋ ላይ ከሚጥል አያያዝ የመጠበቅ መብት እንደሚኖራቸው፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን ተብሎ የሚቋቋመው ተቋምም በዚህ መርህ ብቻ መሥራት እንደሚገባው ሰነዱ በአስገዳጅነት አስፍሯል፡፡

የሚቋቋመው ኮሚሽን የአሠራር ሥርዓቶችና የሚሰጣቸው ውሳኔዎች፣ ወይም የሚፈጽማቸው ተግባሮች ዋና ዓላማ እስረኞች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ታርመውና በመልካም ሥነ ምግባር ታንፀው ሕግ አክባሪ፣ ሰላማዊና አምራች ዜጎች ሆነው ወደ ኅብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ እንደሚሆን ያስቀምጣል፡፡

  “የታራሚዎች አያያዝ በፆታ፣ በዕድሜ፣ በዜግነት፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በታሰሩበት ምክንያት፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ ወይም በሌሎች ማናቸውም መሰል ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ልዩነት ማድረግ የተከለከለ ነው፤” ሲል ረቂቅ የሕግ ሰነዱ ያስረዳል፡፡

ረቂቅ የሕግ ሰነዱ እስረኞች በሁለት የሚከፈሉ መሆኑን፣ እነዚህም በፍርድ ቤት የእስር ቅጣት የተወሰነባቸው ታራሚዎችና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ የተወሰነባቸው እስረኞች መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ማረሚያ ቤት በሕግ ሥልጣን በተሰጠው ፍርድ ቤት የተሰጠ ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ መኖሩን ሳያረጋግጥ፣ ማንኛውንም ሰው መቀበል እንደማይችል በሰነዱ ተመልክቷል፡፡  

እስረኛን በቂ ስፋት በሌላቸውና የተፈጥሮ ብርሃንን ለማስገባት በማያስችሉ መስኮቶች ማስቀመጥ፣ እንዲሁም የጤና ሁኔታን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ መያዝና ምሽት ላይ የኤሌክትሪክ ብርሃን በሌላቸውና የአልጋ፣ የፍራሽና የመኝታ አልባሳት በሌላቸው ክፍል ውስጥ እንዲቆይ ማድረግ ሲከለከል፣ ይህንንም ማረሚያ ቤቶች የማክበር ግዴታ እንደሚኖርባቸው በሰነዱ ሰፍሯል፡፡

በሌላ በኩል ከማረሚያ ቤት ለማምለጥ የሞከረ፣ ዝግጅት ያደረገ፣ በሌሎች እስረኞች ወይም በኮሚሽኑ ሠራተኞች ላይ ጉዳት ለማድረስ የሞከረ ወይም ያደረሰ፣ ወይም የማረሚያ ቤቱን ደንብና ሥርዓት ለማክበር ፈቃደኛ ያልሆነ፣ ወይም የማረሚያ ቤቱን ኃላፊዎችና ፖሊሶች ትዕዛዝ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነ፣ ወይም በራሱ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሞከረ እስረኛ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ በማረሚያ ቤቱ ግቢ ውስጥ በሚገኝ የተለየ የእስር ክፍል ውስጥ እንዲቆይ ሊደረግ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ ነገር ግን እነዚህን እስረኞች ለይቶ የመያዝ ተግባር ከ15 ተከታታይ ቀናት በላይ በተለየ የእስር ክፍል ውስጥ ማቆየትን፣ በጨለማ የእስር ክፍል ውስጥ ማሰርን፣ እንዲሁም በቀን ውስጥ ቢያንስ ከሦስት ሰዓት ላላነሰ ጊዜ ከታሰሩበት ክፍል ውስጥ ወጥተው በክፍት ቦታ ላይ የተፈጥሮ ብርሃን እንዳያዩ መከልከል እንደማይቻል ተካቷል፡፡

እስረኞች ከውጭ ማኅበረሰብ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት በተመለከተ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ከሚፈቅደው ከትዳር አጋሮቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸውና ከመሳሰሉት ጋር ከመገናኘት መብት በተጨማሪ፣ “ሚስጥራዊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ እስረኛው በደብዳቤ ወይም በጽሑፍ የመገኛኘት፣ እንዲሁም በማረሚያ ቤት ቆይታው በኅትመት፣ በምሥልና በድምፅ የሚተላለፉ መረጃዎች የማግኘት፣ ከሚዲያ አካላት ጋር ቃለ ምልልስ የመስጠት መብት ይጠበቅለታል፤” የሚል አንቀጽ በረቂቁ መካተቱን የተገኘው ሰነድ ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም ታራሚዎች ለልዩ ልዩ ማኅበራዊ ችግሮቻቸው ማቃለያ ፈቃድ እንደሚያገኙ ረቂቅ ሕጉ የሚደነግግ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የታመሙ ቤተሰቦቹን በአጃቢ ፖሊስ ወጥቶ የሚጎበኙበት፣ እንዲሁም በቅርብ ዘመዶች የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የመገኘት መብት እንዲኖራቸውና የማረሚያ ቤት ኮሚሽንም ይህንን አሠራር ማመቻቸት እንደሚገባው ሰነዱ ያሳያል፡፡

 የሕግ ሰነዱ ሴት ታራሚዎችንና እስረኞችን በተመለከተ 18 ወራት ያላለፈው ሕፃን ያላቸው በሚሆንበት ጊዜ ልዩ መብቶች እንደሚኖራቸው አካቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል 18 ወራት ያላለፈው ሕፃን አስፈላጊ እንክብካቤ እንዲያገኝ ከእናቱ ጋር አንዲቆይ እንደሚደረግ፣ የማረሚያ ቤት ኮሚሽንም ለዚህ የሚያስፈልገውን በጀት የማሟላት ግዴታ ያለበት መሆኑ ይገኝበታል፡፡

በተጨማሪም ሴት እስረኞች ከማረሚያ ቤት ውጭ የሚኖር ሕፃን ካላቸው በተቻለ መጠን በየጊዜው በአጃቢ ፖሊስ በመውጣት ሕፃኑን የሚጎበኙበትን ሁኔታ፣ ወይም በማረሚያ ቤቱ ግቢ ውስጥ ለዚሁ ዓላማ ተለይቶ በሚዘጋጅ ቦታ እንዲገናኙ እንደሚደረግ ተካቷል፡፡

ሴት እስረኞች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ወቅት ከፆታቸውና ከግል ንፅህና አጠባበቃቸው ጋር በተያያዘ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁሶች ኮሚሽኑ እንዲያቀርብ በሰነዱ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ በሌላ በኩል ሴት እስረኞች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የሚወልዱ ከሆነ ወደ ሆስፒታል ሄደው እንዲወልዱ፣ እንዲሁም ከወሊድ በኋላ መደበኛ የሕክምና ክትትልና እንክብካቤ እንደሚያገኙም ተካቷል፡፡ ማረሚያ ቤቶች የማረም፣ የማነፅና መልሶ ወደ ኅብረተሰቡ የመቀላቀል ዓላማቸውን ለማሳካት እንዲችሉ መልካም ሥነ ምግባር ለተላበሱ፣ ለኅብረተሰቡ አደገኝነት በሌላቸውና አርዓያ ለሆኑ እስረኞች እንደነገሩ ሁኔታ የማበረታቻ ጥቅም የመስጠት መብት በረቂቁ ሰነድ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

በዚህም መሠረት እስረኞችን ከፍተኛ ጥበቃ ካለው ማረሚያ ቤት ወደ ዝቅተኛ ጥበቃ ያለው ማረሚያ ቤት የማዘዋወር፣ የተጠቀሱትን ባህርይ የተላበሱ እስረኞች ከማረሚያ ቤት ውጭ ሄዶ የመሥራትና ለሠሩትም ሥራ የተሻለ ክፍያ እንዲከፈላቸው የማድረግ፣ የፍርድ ጊዜያቸውን በማጠናቀቅ ላይ ያሉ በመልካም ሥነ ምግባራቸው የሚታወቁና ከእስር ቤት የማምለጥ ሥጋት የላቸውም ብሎ ኮሚሽኑ የለያቸውን እስረኞች፣ ያለ አጃቢ ፖሊስ ከማረሚያ ቤት ወጥተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተገናኝተው እንዲመለሱ የመፍቀድ ሥልጣን ለኮሚሽኑ ተፈቅዶለታል፡፡

የማረሚያ ቤት ኮሚሽን የእስረኞችን ሰብዓዊ መብቶች በጠበቀ ሁኔታ መያዙን ለመከታተልና ለመቆጣጠር እንዲቻል የተለያዩ ሥልቶች ተቀምጠዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የውጭ ቁጥጥር ሥልት አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎችና የዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ እንዲሁም በሕግ የማረሚያ ቤትን የመቆጣጠርና የመጎብኘት ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት በማንኛውም ጊዜ ያለ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ማረሚያ ቤቶችን የመጎብኘት፣ ቅሬታ ያላቸውን እስረኞች የማነጋገር፣ የእስረኞችን መዝገብ የመመርመር፣ የማረሚያ ቤት ሠራተኞችን፣ ፖሊሶችንና ኃላፊዎችን የማናገርና ውጤቱን ከማሻሻያ ሐሳብና ዕርምጃ ጋር ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ለሕዝብ የማሳወቅ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡

ከተጠቀሱት ውጪ ለሰብዓዊ መብት መከበር ታራሚዎችንና ተከሳሾችን የአያያዝ ሁኔታቸውን ለማሻሻል በማሰብ የተቋቋሙ የሲቪል ማኅበራትና ሌሎች ለማረሚያ ቤቱ ቀድመው በማሳወቅ፣ ሁኔታዎችን መከታተል እንዲችሉ በረቂቅ ሰነዱ መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ አባል በሆነችባቸው ወይም በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት የተቋቋሙ ኮሚሽኖች፣ ኮሚቴዎች፣ ሪፖርተሮችና የመሳሰሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሲፈቀድ ማረሚያ ቤቶችን የመጎብኘትና የመመርመር ሥራ እንዲያከናውኑ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች ተካተዋል፡፡

በሌላ በኩል እስረኞች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መብቶቻቸው እንዲጠበቁ በሕግ ከመደንገግ ባለፈ፣ መብቶቻቸው ሲጣሱ ፍትሕ የማግኘት መብት እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ድንጋጌዎች እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

በዚህም መሠረት የመብት ጥሰቶችን አስመልክቶ አንድ እስረኛ ላቀረባቸው ቅሬታዎች በኮሚሽኑ መልስ ካላገኘ ወይም ውድቅ ከተደረገበት፣ ቅሬታውን ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሁለት ወራት ውስጥ ሊያቀርብ የሚችልበት ድንጋጌ በረቂቅ ሰነዱ ተካቷል፡፡

Recommended For You

About the Author: admin