አቶ ሽፈራሁ ሽጉጤ ከደኢህዴን ሊቀ መንበርነት ተነሱ

BBN – የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ወይም ደኢህዴን ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ሽፈራሁ ሽጉጤ ከስልጣን ተሰናበቱ፡፡ አቶ ሽፈራሁ የድርጅቱ ሊቀ-መንበር ሆነው የተመረጡት ከሶስት ወራት በፊት ሲሆን፤ ከእሳቸው በፊት የፓርቲው ሊቀ መንበር የነበሩትን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን በመተካት ነበር ወደ ሊቀ መንበርነቱ የመጡት፡፡ አቶ ሽፈራሁ ከፓርቲው ሊቀ-መንበርነት የተነሱት በገዛ ፈቃዳቸው እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡ ከዚህ ቀደም በደቡብ ክልል ስብሰባ በማካሄድ የሚታወቀው ደኢህዴን፤ አሁን ባልተለመደ መልኩ አዲስ አበባ በሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡

አቶ ሽፈራሁ ሽጉጤ ራሳቸውን ከፓርቲው ሊቀ-መንበርነት አገለሉ የተባሉት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጽ/ቤት በተደረገው የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ ሶስት የደቡብ ክልል ከተሞች ተገኝተው ከነዋሪዎች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል፡፡ ወልቂጤን ጨምሮ በሐዋሳ እና ወላይታ ሶዶ ከተሞች ተገኝተው ከነዋሪዎች ጋር የተወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በወልቂጤ የውይይት መድረክ ላይ፣ ግጭት የተከሰተባቸው ሶስቱ ከተማ የስራ ኃላፊዎች በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣን እንዲለቅቁ ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡

የደቡብ ክልል አስተዳዳሪ የሆነው ደኢህዴን ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ሽፈራሁ ሽጉጤ፤ ራሳቸውን ከሊቀ መንበርነት ማግለላቸውን ያስታወቁት፤ ዶ/ር አብይ አህመድ በወልቂጤ ከተማ ከሰጡት ማሳሰቢያ አንድ ሳምንት በኋላ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ አቶ ሽፈራሁ በቀርቡ በተዋቀረው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔ አማካይነት የግብርና እና የእንስሳት ሀብት ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ተሹመው ነበር፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ራሳቸውን ከደኢህዴን ሊቀ-መንበርነት ቢያገልሉም፤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ በዶ/ር አብይ አህመድ አማካይነት በቅርቡ አቶ አባዱላ ገመዳን በመተካት የፓርላማ አፈ-ጉባኤ ሆነው የተመረጡት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አቶ ሽፈራሁ ሽጉጤን በመተካት የደኢህዴን ሊቀ መንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡

Recommended For You

About the Author: admin