ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት ማቆም አትችልም!

አለመግባባቱ ወደ ግጭት ያመራል የሚል ስጋት በመጫሩ ዕለተ ሐሙስ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ጉዳዩን ይዞ በጠረጴዛ ዙሪያ ሊመክር ነው።

ግብፅና ሱዳን፤ ኢትዮጵያ ብቻዋን መክራ ሁለተኛውን ዙር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ጀምራለች ሲሉ ያማርራሉ።

ለውሃ ፍላጎቷ የአባይ ወንዝ ላይ ጥገኛ የሆነችው ግብፅ የኢትዮጵያን ውሳኔ እንደ ሕልውና ፈተና ነው የምታየው። ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ለሕዝቧ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ስትል የገነባችው ግድብ ውሃ መያዙን ተከትሎ ሱዳን ወደኔ የሚፈሰው ውሃ ቀንሷል ብላ ነበር።

በዚህ ሳምንት መባቻ መግለጫ የለቀቁት ግብፅና ሱዳን፤ ኢትዮጵያ ማንንም ሳታማክር ውሃ መሙላት መጀመሯ “በክፋት ነው” ነው ሲሉ ወቅሰዋል። ይህም ኢትዮጵያ ሆን ብላ ነው ግድቡን የሞላችው የሚል ሐሳብ አለው።

ነገር ግን ይህ የሁለቱ ሃገራት ወቀሳ ግድቡን መሙላት ማለት አንድ ባሊ እንደመሙላት ያለ ያስመስለዋል። ልክ ኢትዮጵያ የቧንቧው ባልቦላ በእጇ እንዳለ ያለ ያክል ምስል ይሰጣል።

ማስቆም ይቻል ይሆን?

አይቻልም። ከግድቡ ጀርባ ያለው ውሃ ማቆሪያ ጉድጓድ በተፈጥሯዊ መንገድ የሚሞላው በዝናባማ ወቅት ነው። ክረምቱ ደግሞ ገብቷል፤ እስከ መስከረም እንደሚቆይም እሙን ነው።

የአባይ ግድብን ላለፉት 10 ዓመታት ሲያጠኑ የነበሩት የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲው ሞሐመድ ባሽር አሁን ግንባታው ከደረሰባት ደረጃ አንፃር “በኢንጂነርንግ አሊያም በፊዚክስ ሕግ ካየነው ሙሌቱን ማስቆም የማይቻል ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ይህ የሚሆንበት አንደኛው ምክንያት ከዚህ በፊት ዘልቆ የሚሄደው ውሃ አሁን ግን ማቆሪያውን ሞልቶ ነው ወደ በሁለቱ ቀዳዳዎች የሚያልፈው።

ግንባታው ከተጀመረበት የፈረንጆቹ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ግድቡ በአባይ ወንዝ ዙሪያ ነው ሲገነባ የነበረው። ይህም ወንዙ ወደ ታችኛው ተፋሰስ ሃገራት መፍሰሱን እንዲቀጥል በማሰብ ነው።

ወንዙ መጠኑን በሚቀንስበት ሞቃታማ ወራት አቅጣጫውን ቀይሮ ወደታች እንዲፈስ ተደርጎ ደግሞ መሃል ላይ ግንባታው ይከናወናል።

አሁን መሃል ላይ ተሰድሮ የሚታየው የግድቡ ግዙፍ አካል ወደመጠናቀቁ ደርሷል። ከፍታው ከባሕር ወለል በላይ 640 ሜትር እስኪደርስ ድረስ ይቀጥላል።

ቀጣዩ ክፍል ምንድነው?

በመጀመሪያው ዓመት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ አከማችቷል።

በአማካይ በየዓመቱ በሕዳሴው ግድብ አቋርጦ የሚፈሰው የዓባይ ወንዝ መጠን 49 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው። ነገር ግን ባለፈው ዓመት በ100 ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የውሃ መጠን ተመዝግቧል። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ግድቡ ከዓመታዊው ፍሰት ይዞ የሚያስቀረው በጣም ጥቂት ውሃ መሆኑን ነው።

በዚህ ዓመት የታቀደው 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለማከማቸት ቢሆንም በሱዳን በኩል ያሉ የሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳዩት ግድቡ ይህን ውሃ ማቆር የሚያስችል ድረስ ስላልተገነባ በዚህ ዓመትም ከበቂ በላይ ውሃ ወደታችኛው ሃገራት መፍሰሱ አይቀርም።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ውሃ ሚኒስቴር ለሱዳን በላከው ደብዳቤ ላይ ግድቡ ልክ መጀመሪያ እንደታሰበው የታቀደውን ያክል ውሃ እንዲያከማች ተደርጎ መሠራቱን ይቀጥላል።

ኢትዮጵያ እንደምትለው ግድቡ በሚቀጥሉት ከአራት እስከ ስድስት ዓመታት ተገንብቶ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንዲያቆር ይደረጋል። የዚያን ወቅት የሚፈጠረው ሐይቅ እስከ 250 ኪሎ ሜትር ድረስ ሊዘረጋ ይችላል።

ግብፅ ለምን ተቆጣች?

ግብፅ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን እንደ ሕልውና ጠር ነው የምታየው። በዓባይ ግድብ ላይ ጥገኛ የሆነችው ግብፅ በላይኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚከናወነውን በሙሉ በንቃት ትከታተላለች።

ግብፅ ወደታች የሚፈሰው ውሃ መጠን ላለመጓደሉ ማረጋገጫ ትፈልጋለች።

በውሃ ሙሌቱ ወቅት ግብፅ የጎደለባትን ውሃ ከሃይ አስዋን ግድብ ላይ በመቀነስ መሙላት ትችላለች። ነገር ግን ዋናው አሳሳቢ ጉዳይ የሚመጣው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ነው።

ግብፅ ውሃ ሙሌቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያ ወደታች የምትለቀውን ውሃ ልትቀነስ ትችላለች የሚል ፍራቻ አለባት። ኢትዮጵያ ዋነኛ ትኩረቷ የሚሆነው ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ትልቁ ኃይል አመንጪ የሚሆነው ግድብ መሙላቱ እንጂ ጎረቤት ሃገራት አይደሉም ትላለች።

ዝናቡ መጠኑ ባልቀነሰበት አሊያም በጨመረበት ወቅት ወደታች የሚፈሰው ውሃ ጉዳይ አሳሳቢ አይደለም። ነገር ግን ግብፅ ለዓመታት የሚዘልቅ የድርቅ ወቅት በሚጣበት ወቅት ምን ይሆናል የሚለው ያሳስባታል።

ኢትዮጵያ በዚህ የድርቅ ወቅት የአባይ ግድብ ውሃን የምትይዝ ከሆነ ግብፅ ወደ ሃይ አስዋን ግድብ ፊቷን ማዞሯ አይቀርም። ግድቡም የውሃ መጠኑ እየቀነሰ ይመጣል።

ሱዳንስ?

ባለፉት 12 ወራት የሱዳን አቋም ሁሉንም እጅን ዘርግቶ ከመቀበል ወደ ተጠራጣሪነት አምርቷል።

ባሽር ይህ የሱዳን የአቋም ለውጥ የመጣው ባለፈው ዓመት የተካሄደውን የውሃ ሙሌት ከተመለከተች በኋላ ነው ይላሉ።

በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ወደ ሱዳን የሚወርደውን ውሃ በመቆጣጠር ሱዳንን ካልተጠበቀ ጎርፍ ሊገላግላት ይችላል።

ነገር ግን ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ከአራቱ የግድቡ የውሃ ማለፊያ ቀዳዳዎች ሶስቱን ስትዘጋ ሱዳን ሳትደነቅ አልቀረችም።

Recommended For You

About the Author: admin