ደብዳቤ ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ::

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሬፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ለክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
አዲስ አበባ

በሚያነቡ አይኖች ላይ የደስታን ፀዳል እንዲሁም በተፈናቀሉና በግፍ በተጨፈጨፉ ወገኖቻችን የሐዘን ጥላ በአጠላበት መጠለያ ታዛ ውስጥም የሳቅ ድምፅ አይሰማም !


ክቡር ሆይ
በተቀዳሚ በዚህ እጅግ ፈታኝ በሆነ የትንንቅ ወቅት ፣ ከመላው አውሮፓ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን ወገኖችዎ የሐገርን ልዑላዊነትና የወገኖቻችንን ደሕንነት ለማረጋገጥ በአካልና በሕይወት ጭምር መሥዋዕትነትን በመክፈል ላይ ላሉ ሁሉ ያለንን አድናቆትና ክብር ለመግለፅ እንወዳለን ።
ክቡርነትዎ በቅርብ እንደሚያውቁት ከመሥሪያ ቤትዎ የወረደ ነው በተባለለትና በጥቂት የአውሮፓ ኤንባሲዎች ብቻ በተበተነ የመስሪያ ቤትዎን አርማ በያዘ ይፋ ደብዳቤ መሠረት ለአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ቤተሰብ የዕርዳታ እጃችንን እንድንዘረጋ ተጠይቀናል ።
በመሠረተ ሐሳቡ እንኳን በአሸባሪዎች ጥይት ሕይወቱ በአጭር ለተቀጨበት ወገናችን ቤተሰብ ቀርቶ በተፈጥሮ ሞትም ቢሆን ለተለየ ማንኛውም የሰው ልጅ ሁላ ማሕበረሰባችን ያለውን ሐዘንን የመግለፅ ባሕልና ወግ እንዲሁም መረዳዳት በግልፅ የሚታወቅ ሃቅ ነው ።
ክቡርነትዎ በቅርብ እንደሚያውቀው ሁሉ የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን በፅንፈኛ ሽብርተኞች መገደልን ተከትሎ ወዲያውኑ ምንም ከሁኔታው ጋር ግንኙነት በሌላቸው ምስኪን ወገኖቻችን ላይ በተከተለው መጠነ ሰፊ የግድያና ንብረት የማውደም የተቀነባበረ ዘመቻ የተነሳ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ንፁሓን ወገኖቻችን ላይ እጅግ አስከፊና ዘግናኝ ጭፍጨፋ ደርሷል !
በተለይ በሻሸመኔ፣በአርሲ ነገሌ፣በዝዋይ፣በኮፈሌ፣በአጋርፋ፣በአጄ፣ በምዕራብ ሐረርጌና በሌሎችም በስም ባልጠቅስናቸው የአገራችን ከተሞች ውስጥ የተፈፀመው አረመኔያዊ ፍጅትና ጥፋት በባሕሪውና በአፈፃፀሙ ዘግናኝነት አንፃር ሲመዘን ፋሺስታዊ የዘር ማፅዳት ወንጀል መሆኑን እያደር ለሕዝብ ዕይታ የቀረቡ የአውዲዮ ፣ የቪድዮ ምስሎችና የሰው ምስክርነቶች በማያወላዳ ማስረጃነት ይመሰክራሉ ።
ክቡር ሆይ
በመላው አለም ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ገና አሰቃቂ ከሆነው ከዚህ የወገን ፍጅትና ሐዘን ሳይላቀቅና ሳይፅናና እንዴት አድርገንም ለወገኖቻችን እንድረስላቸው እያለ በሚብሰለሰልበት ወቅት በተለይም በመንግሥት በኩል አንድ ጉዳተኛ ወገኖቻችንን የምንረዳበት ማዕከል ተፈጥሮ ቢያንስ የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ እንችላለን ብሎ በሚጠብቅበት ሰዐት በጥቂት ለጋስ ሰዎችና በፈቃደኛ ዜጎች ብቻ እዚያው ሐገር ቤት ሊከወን የሚችለውን የአንድ ቤተሰብ ድጋፍ ብቻ ነጥሎና በሺህ ከሚቆጠሩ ንፁሐን የአሽባሪ ሰለባ ወገኖቻችን ጉዳት በላይ አጉልቶና ተቀዳሚ አድርጎ ዕርዳታ በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በኤንባሲዎች ይፋዊ ደብዳቤ ዕርዳታ መጠየቅ እጅግም አድርጎ አሳፋሪና ፕሮቶኮሉንም ቢሆን የተከተለ አሠራር ነው ብለን በፍፁም አናምንም ።
ክቡር ሆይ
እንደነዚህ አይነቶች ስሜትን በቀላሉ የሚጎዱና ከፈረሱ በፊት ጋሪውን የሚያስቀድም አሠራር በጣም ግልብና ሊያስከትል የሚችለውንም አሉታዊ ውጤት ያላገናዘበ መሆኑን ዲፕሎማቶቻችን እንዴት ሊገነዘቡት እንዳልቻሉ በጣም አስገርሞናል ። ይህ አይነት አሠራርም የጠቆመን ነገር ቢኖር በተደጋጋሚ የውጩን የዲያስፖራ ማሕበረሰብ በማስተባበር ብዙ ሐገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች ለመከወን ብቃትና ልምድ ባላቸው ዲፕሎማቶች ድርቀት የውጩ ኤንባሲዎቻችን ክፉኛ እንደተመቱ ነው።
በመጨረሻም በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ መነሳሳትና ቁርጠኝነት እየተካሄደ ያለውን የውስጥ ምንደኛንና የውጭ ፀረ ኢትዮጵያ ሐይሎችን ሤራ የማምከን ቆፍጣና እርምጃ በሙሉ ልባችን የምንደግፍውና በሁሉም ረድፍ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጎን በመቆም ለሕግ የበላይነት፣ለሐገር ልዑላዊነትና ለጋራ ብልፅግና ለመሥራት የተነሳሳን መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን ።


ግልባጭ
ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

ኢትዮጵያ በልጆችዋ መሥዋዕትነት ተከብራ ትኖራለች !
አባይ ይገደባል የጠላቶቻችንም ሤራ ይከሽፋል !
የኢትዮጵያዊያን ማሕበር በአውሮፓ !


Recommended For You

About the Author: admin